top of page
Writer's pictureHager Bekel

“መተንፈስ አልቻልሁም”:- የነጭ ሉአላዊነት ስርአት አለማቀፋዊ ገጽታ

የሰሞኑ ዜና፡- “ጆርጅ ፍሎይድ የተባለውን ጥቁር አሜሪካዊ ደረክ ቻቭን የተባለ ፖሊስ አንገቱን ረግጦ ገደለው”። ይህ ዘግናኝ ዜና የራሱ የሆነ በተለይ አሜሪካን የሚመለከት ትርጉም እንዳለው አይካድም። የአንድ ሰው መሞት በቤተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ህመምና ለእኛ የሚሰጠን ትርጉም እኩል አለመሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። እንደግለሰብ የፍሎይድ መሞት በተለይ ለቤተሰቡ በቃላት የማይገለጽ ሁኔታ ልብ ይሰብራል። ሆኖም ፍሎይድ የተገደለበት ምክንያት እንደግለሰብ ስላጠፋ አይደለም። ፍሎይድ የሞተው የጥቁርነትን ሰብአዊ ክብር መርገጥ የሚቻልበት አለማቀፍ ስራት ስላለ ነው። ግድያው የአሜሪካ ስራት በሁለት ዘሮች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስተናግድበት ተግባራዊ ማሳያ ቢሆንም፣ ዘር ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ፣ ይህ ድርጊት አለማቀፍ ትርጉም አለው። ይህ ድርጊት በምድራችን ላይ የተንሰራፋው የነጭ ሉአላዊነት ስራት ጭምብሉን ገለጥ አድርጎ ለአለም በግልጽ ሲታይ ምን እንደሚመስል ያየንበት አጋጣሚ ነው።


ድርጊቱን ከግለሰብ ድርጊት ባሻገር እንመልከተው። አንድ ህግ አስከባሪ ፖሊስ በአለም ፊት በቪዲዮ እየተቀረጸ፣ ጎዳና ላይ በጓደኞቹ ታጅቦ፣በኩራት እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ፣ ምንም ያላጠፋና በካቴና የታሰረን ሰው፣ አንገቱን እረግጦ ሊገለው የሚችልበት ሁኔታ እንዴት ሊኖር ቻለ? ይህን ድርጊት ተደጋግሞ እንዲፈጸም የሚያደርገው ሁኔታ ምን ስላለ ነው? ጉዳዩን ከገዳይና ከሟች ባሻገር ማየት ያስፈልጋል። የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በጥቁር ዘር ላይ ሲፈጸም የነበረ ግድያ ተከታይ ታሪክ ነው። ባለፉት አንድ መቶ አመታት ውስጥ ብቻ በደቡብ አፍሪካ፣ በኮንጎ፣ በሞዛምቢክ፣ በናሚቢያ፣ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በአልጀሪያ ወዘተ ጥቁሮች በቅኝ ገዢወችና በፋሽስቶች ተገለዋል። ዛሬም በአፍሪካ ውስጥ የሚፈሱት ደሞች የነጭ ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ከተዘረጋው አለማቀፍ የካፒታሊዝም ስራት ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ስለዚህ የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ አካላዊ ግድያ ስለሆነ ትኩረት ቢያገኝም የግድያው ታሪካዊ ስርና መሰረት የሆነው የነጭ ሉአላዊነት ስራት ምን እንደሆነና ከእኛ ጋር ምን እንደሚያገናኘው መመርመር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ዘረኝነት የነጭና የጥቁር ግለሰቦች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ የሆነ የስራት ባህሪ መገለጫ ስለሆነ ነው።


የነጭ ሉአላዊነት ማለት በእውቀትና ባስተሳሰብ፣ በእምነትና በተግባር፣ በፖሊሲና በገንዘብ ወዘተ ከአካባቢ እስከአለማቀፍ ድረስ የነጮችን የበላይነትና ጥቅም የሚያስጠብቁ ሃሳቦችና አሰራሮች የሰፈኑበት ስርአት ማለት ነው። ይህ ስርአት አሜሪካ ወይም አውሮፓ ብቻ አይደለም ያለው። ይህ ስርአት አለማቀፍ ስርአት ሆኖ ብዙ ሃገሮች የሚገዙለት ስራት ነው። የነጭ ሉአላዊነት ስራት ከተመሰረተ ወደ አምስት መቶ አመታት ይጠጋዋል። በአለማችን ትንሺ ከሆነችው የአውሮፓ አህጉር ተነስቶ፣ ሶስት አህጉሮችን ከባለቤታቸው ቀምቶ ለነጮች መስፈሪያነት ሰጥቷል፦ መጀመሪያ ደቡብ አሜሪካ፣ ከዛ ሰሜን አሜሪካና ካናዳ፣ ከዛም አውስትራሊያና ኒውዚላንድ። የእነዚህ አህጉሮች ባለቤት የነበሩትን ጥንታዊ ህዝቦች በግፍ አስወግዷል፤ ጉልበታቸውን በዝብዟል። ይህ ስርአት ምህረትና ፍትህ የሚባል ነገር አያውቀውም። በጭራሽ አሁንስ ይበቃናል፣ በእኩልነትና በፍቅር እንኑር ብሎ ተግባራዊ ለውጥ አያደርግም። ዘራቸውን የጨፈጨፈባቸውንና ሃገራቸውን የቀማቸውን ያሜሪካ ህንዶችና አቦሪጅኖች፣ በባርነት እያሰራ የከበረባቸውን ጥቁሮች ሌላው ቀርቶ ይቅርታ አላላቸውም፤ ካሳ አልሰጣቸውም። እንደውም የልጅ ልጆቻቸውን ሳይቀር በእስርና በአስከፊ ድህነት ላይ አሁንም እንዲኖሩ አድርጓል። መቶ ሚሊዮን የሚደርሱ የአሜሪካ ህንዶችን ጨፍጭፏል፤ እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪካውያንን በባርነት ወስዶ ከህንዶች የዘረፈውን አህጉር አስለምቷል። ባርነት አላስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ደግሞ አፍሪካውያንንና እስያውያንን በቅኝ ግዛት በዝብዟል። ይህንን እያደረገ ከፍተኛ ሃብት ያከማቸው የነጮች ሉአላዊ ስራት ከ2ኛው ያለም ጦርነት በኋላ የነጮችን ጥቅምና ክብር የሚያስከብሩ አለማቀፍ ተቋማትን በመፍጠርና ገለልተኛ በማስመሰል የግሎባላይዜሽን ስራት ፈጥሯል። አለማቀፍ ሰባዊ መብት በደነገገ ማግስት በደቡብ አፍሪካ ያፓርታይድ ስራት ፈጥሯል። ቅኝ ይገዛቸው የነበሩት ሃገሮች ውስጥ በጥቅም ከነጮቹ ጋር የተሳሰሩ ሃገርበቀል ቅኝ ገዢወችን ተክቶ ጥቅሙን በማስከበር ላይ ይገኛል። መሰልጠን ማለት ነጮችን መከተል እንደሆነ አድርጎ በትምህርት ስራት በማሳመን፣ ዛሬም ድረስ በያገሩ የነጮችን እግር እያነፈነፉ ህዝባቸውን ይዘው የሚከተሉትን መንግስታትና ምሁራን አፍርቷል። አረመኔነቱ ተረስቶ ጨዋና አራያ ሆኖ መታየት ጀምሯል። ይህ የነጮች ሉአላዊ ስራት በይፋ የሚታወቅበት ስም ካፒታሊዝም ይባላል። አህጉሮችንና ህዝቦችን ለ500 አመታት በመዝረፍ ካፒታልና ሌላም ሃብት እንዴት እንዳከማቸ ሳይሆን በሳይንሳዊ ምርምርና እውቀት እንዴት እንደሰለጠነ የሚያስተምር ትርክት (ቲወሪወች) በመፍጠር የድሃ ሃገራት ልጆች ታሪኩን ረስተው ቲወሪውን እንዲያምኑ በማድረግ፣ የአስተሳሰቡ ተከታይና የጥቅሙ ተስፈኛ አድርጓቸዋል። በኢኮኖሚውም እድገት ማለት የተፈጥሮ ሃብትን ወደ ዶላር መቀየር እንደሆነ እንዲሆን፣ ትምህርት ማለት ፈረንጆቹ ያወቁትን ማወቅ እንደሆነ አድርጎ በማሳመን፣ ድሃ ህዝቦች ህይወታቸውን በማይቀይር ልማትና ትምህርት ላይ ሃብታቸውን እንዲያፈሱ አድርጎ፣ በድህነት ላይ ራሳቸውን እየረገሙ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።


የነጭ ሉአላዊ ስራት ነጭ ህዝቦች እንደግለሰብ በጥቁሮች ላይ የሚፈጽሙት ድርጊት ሳይሆን የአስተሳሰብና የሃይል አሰላለፍ መመሪያ ነው። የትም ይሁን የት፣ ማንኛውም ሃገርና ህዝብ እድገትና መሻሻል እንዲያመጣ ከፈለገ የነጮችን ሉአላዊነት የሚያስጠብቅ ስርአት እንዲከተል ይደረጋል። ይህ ማለት የትምህርትና የልማት ፖሊሲው የነጮችን አመለካከትና ፍላጎት የሚያከብር መሆን አለበት ማለት ነው። የተዘረጋው የንግድና የብድር ህግ ሁሉ በልማትና በእርዳታ ስም ይህንን ያስፈጽማል። ሌላው ቀርቶ ከድሃ ህዝብ በተወሰደ ገንዘብ በነጻ የምንማረው ተማሪወች እንኳን አስተሳሰባችን የሚቀረጸው በዚህ ስርአት እምነትና ህግ ነው። የህዝባቸንን ቋንቋና አስተሳሰብ ተትን በፈረንጆቹ ቋንቋ የነሱን ሃሳብ ስንማር የነጭ ሉአላዊ ስራት አማኞች እንድንሆን እየተደረግን ነው። የነሱን ታሪክ እናጠናለን፤ የእኛን ባለበት እንዲቆምና እንዲጠፋ እናደርጋለን። ይህንንም ስናደርግ ትክክለኛውን የነሱን ታሪክ ሳይሆን የነጮችን ሉአላዊነት የሚሰብኩ ፍልስፍናወችንና ትርክቶች ብቻ ነው እንድናውቅ የሚደረገው። በየትኛውም ታላላቅ ዩንቨርስቲ ውስጥ የነጮች ሉአላዊ ስራትን ኢፍትሃዊነት በግልጽ የሚያስተምር የትምህርት ዘርፍ የለም። ዘረኛ የነበሩትን እነ ሄግልን፣ ዳርዊንን፣ ሎክን፣ ካንትን፣ ሚልን፣ ሩሶን ወዘተ እንደሰው ልጆች ሁሉ ምሁራን አድርገን እንማራለን፤ ነፍሰገዳይ የነበሩትን እነኮሎምበስን አዲስ ግኝት ያመጡ አድርገን እናጠናለን። እነዚህ ሁሉ ሰወች ነጭ ስላልሆኑት ሰወች የተናገሩትን ዘረኛ አስተሳሰብ ማንም አያስተምረንም።


ሁለት ምሳሌወችን እንይ። የምራቡ አለም ዘረኝነትን የተፈጥሮ ህግ አድርጎ እንደሳይንስ ለማቅረብ ከተጠቀመባቸው ንድፈሃሳቦች (ቲወሪወች) አንዱ የቻርለስ ዳርዊን ትርክት ነው። ይህ ትርክት የሰው ልጅ ከዝንጀሮ ተነስቶ በዘግምተኛ ለውጥ እንዴት ነጭ እንደሆነ የሚያሳይ ንድፈሃሳብ ነው። ይህ ትርክት መላ ምት እንጅ የተረጋገጠ ታሪክ አይደለም። ሆኖም ጥቁሮችን ከዝንጀሮ ጋር በማቀራረብ የነጮችን ሉአላዊነት የሚያስከብር አንድምታ ስላለው አለማቀፍ ሳይንሳዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደርጓል። ነጮቹ የሚቀበሉትን ነገር እንደእውቀት ሽልማት የሚያየው የእኛ ሰው ደግሞ፣ ሃሳቡን ከዘረኝነት ማራመጃነቱ ሳይለይ እንዳለ ሳይንስ አድርጎ ልጆቻችንን ያስተምራል። በአምስት ኪሎ ቤተመዘክራችን እንዳለው የሉሲ ዘጋቢ ፊልም ትርክቱን በኩራት ለእይታ ያቀርባል። እዚህ ላይ ሰው ከዝንጀሮ መሰል ነገር መጣ አልመጣም ብለን ለመከራከር አይደለም። እውነትም ይሁን ውሸት ቁም ነገሩ ከአለማቀፉ የነጮች ሉአላዊ ስራት ጋር ይህ ትርክት ያለው ታሪካዊና ነባራዊ ትሥስር ጠንካራ መሆኑን ማወቁ ላይ ነው። በአሁኑ ዘመን በሂትለር የሚሰየም ሆቴል ወይም ሙዚየም ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ሂትለር 6 ሚሊዮን አይሁዶችን በግፍ ገሏል። የቤልጀሙ ሊዮፖልድ ከሂትለር ያልተናነሰ አረመኔያዊ ድርጊት በአፍሪካውያን ላይ ፈጽሟል። ከ8-10 ሚሊዮን የሚደርሱ የኮንጎ ህዝቦች በሊዮፖልድ አገዛዝ አልቀዋል፣ የቀሩት በግፍ ተበዝብዘዋል። ታዲያ ግን ያፍሪካ መዲና የሆነችው አዲሳበባ ላይ በሊዮፖልድ የተሰየመ ባለክብር ሆቴል ተሰርቷል። በፋሺስቱ ሂትለር ለሞቱት አይሁዶች አለም ያለቅሳል፤ በፋሽስቱ ሊዮፖልድ ለሞቱት ጥቁሮች ግን ትዝታ እንኳን ብርቅ ነው።


የነጮች ሉአላዊ ስራት መገለጫወች ብዙ ናቸው። አንዳንድ ምሁራን አልፎአልፎ ይህንን ለማጋለጥ ታግለዋል። ግን ሰሚና ደጋፊ አያገኙም። ብዙ ምሁራን የጻፉትንና የተናገሩትን ካየን ደግሞ እንገረማለ። እነዚህ ምሁራን አስገራሚ በሆነ ደረጃ የነጮች ሉአላዊ ስራት ምን አይነት ታሪክ፣ ባህሪና ድርጊት እንዳለው አያውቁም ብሎ መናገር ይቻላል። በልዩ ልዩ አጋጣሚ የሚገለጽላቸው ሁኔታ ሲፈጠር እንኳን ያለፈ ስህተት አድረገው ያዩታል፤ ወይም የራሳቸውን ክብር የሚያሳንስ መስሎ ስለሚሰማቸው ያቃልሉታል፣ ወይም እንዳያውቁትና እንዳያሳውቁት የሚያደርግ ተቋማዊ ተጽእኖ ይደርስባቸዋል። የነሱ ምሁራዊ ሰብእና ወደፈረንጆች አስተሳሰብ በመጠጋት የተገኘ ስለሆነ፣ ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነጮች የሚያንቋሽሽን ነገር ሁሉ በነሱ ክብር ወይም እንጀራ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው የሚያዩትም አሉ። በነጮቹ የትልቅነት ምስል ተጠልለው ባገራቸው ህዝብ ውስጥ መከበር ስለለመዱ፣ በፈረንጆቹ ላይ የሚሰነዘር ትችትን መታገስ ይከብዳቸዋል። ከህዝባቸው እኩል መሆን መዋረድ፣ ከፈረንጆች እኩል መሆን ደሞ መከበር መስሎ ይታያቸዋል።


ይህ ጥገኝነት በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በሃገር ደረጃም የሚታይ ነው። የነጮች ሉአላዊነትን የሚያገለግሉ ሃገራዊ ስርአቶች የሃገራቸውን ምርጥ ምርጥ ነገር ሁሉ ለነጮች ገበያ ለማቅረብ ይጥራሉ። ለምሳሌ የሚገነቡት ውብ ሆቴሎች፣ የቱሪስት ቦታወች፣ የማእድን ቦታወች፣ ታላላቅ የልማት አውታሮችና አንዳንዴም የሚታረሱት መሬቶች ሳይቀር ታሳቢ ተደርገው የሚሰሩት የነጮችን የገበያና የውበት ፍላጎት ነው። ምንም እንኳን ሃገራዊ ጥቅም ለማግኘት ይህ ተግባር አስፈላጊ ነው ብለን ብናልፈውም ተግባሩ የሚሰራበት ስነልቦና የተቃኘው ግን የፈረንጆችን ሉአላዊነት በመቀበል ነው። በ6ቱም አህጉሮች ውስጥ ከጥቁሮች ጋር ተመሳሳይ ክፍያ ከፍለው፣ ባንድ ቦታ ነጮችና ጥቁሮች ቢቀመጡ፣ የበለጠ ክብርና መስተንግዶ የሚሰጠው ለነጮች ነው። እያንዳንዱ ሰራተኛ የነሱን ቋንቋ የሚናገር መሆን አለበት። በግሎባላይዜሽን ዘመን ፈረንጆች በቀላሉ የሃገራትን ድንበር በፓስፖርታቸው ተሻግረው፣ ምርጥ ምግብ ተመግበው፣ ምርጥ ሆቴል ውስጥ ተኝተው፣ ምርጥ ነገር አይተው፣ ያላፊ አግዳሚዉን ፈገግታ ጠግበውና የፈለጉትን አድርገው ወዳገራቸው ይመለሳሉ። ኑሮና ጭቆና የመረራቸው ወገኖቻችን ግን ህይወታቸውን ለማትረፍ ተሰደው በባህር ሲጓዙ ውቅያኖስ ላይ ሰምጠው ያልቃሉ ወይም ይታሰራሉ። ብርቅየ እንሣትን መግደል የፈለገ ጥጋበኛ ፈረንጅ አፍሪካ መጥቶ ገንዘብ ከከፈለ እንክብካቤ እየተደረገለት ብርቅየውን እንስሣ እንዲገል ይፈቀድለታል። አንድ ድሃ አፍሪካዊ ግን (በሰረንጂቲ ፓርክ እንደታየው) ለአደን ወጥቶ እንስሳ ቢገድል የቱሪዝም ሃብት አጠፋ ተብሎ ይታሰራል። የእነሱ መንግስታት በሚያትሙት ዶላር ምድር ላይ የማይገዙት ነገር የሌለ ይመስላል።


ይህ ሁሉ የሚያሳየን አለማችን ውስጥ ጥቅምን ከራስ ሉአላዊነት በላይ የሚያዩ ባህሎችና አሰራሮች መንገሳቸውን ሲሆን፣ ጥቅም የሚገኘው ደሞ የነጮችን ሉአላዊነት በማስከበርና በማክበር እንዲሆን ስለተደረገ፣ በተዘዋዋሪም ቢሆን ሁላችንም የነጮች ሉአላዊነት ስራት ተገዢ እየሆን መምጣታችንን ነው። እዚህ ላይ አንዳንዶች ሌላ ምን አማራጭ አለ ብለው ጥያቄ ያቀርባሉል።፡ነገር ግን ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁት ሰወች በነጮች ሉአላዊ ስራት ውስጥ ለነሱ የሚሆን አማራጭ ያገኙ ወይ ተስፋ ያደረጉ ሰወች ናቸው። እነሱ የያዙትን አማራጭ እንጅ በነጮች ስራት አማራጭ ያጡትንና አዲስ አማራጭ ለመፍጠር የማይችሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻቸውን ዞር ብለው አያዩም። እንዴት ነው መቶ ሚሊዮን ህዝብ በፈረንጅ ቋንቋ ተምሮ የሚሰለጥነው? የነጮች ሉአላዊ ስራት ዋናው አላማ ሃገርበቀል አማራጭ እንዳይኖር ማድረግ ነው። በዚህ ስራት ውስጥ እሳከለን ድረስ በሃገራችን ምርትና ባህል እየተጠቀምን እንኳን፣ “አይቀርልንም!” በሚል፣ ገና ለገና ህይወታችን ሙሉ በሙሉ በነጮች ጥገኛ ሳይሆን ቀድመን እጅ እንሰጣለን። በራሳችን እጅ አዲስ ነገር ፈጣሪ የሆነውን አእምሮአችንን በሰንሰለት እናስራለን። ስርአቱ የአስተሳሰብ እስር ቤት ነው። ሃገርበቀል ቅኝ ገዢወች ኑሯቸውን የመሰረቱት ካገራቸው ፍላጎት ተጻራሪ በሆነ የኢኮኖሚ ተግባር ተሰማርተው ስለሆነ የእነሱን አማራጭ ማጣት የህዝብ አማራጭ ማጣት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ።


የኢኮኖሚውን እንተወውና በአካል ራሱ የነጮች የበላይነት በበርካታ መንገድ ባገራችን ይገለጻል። ብዙ ባይወራላቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዘግናኝና አሳፋሪ ተግባራት በነጮች ሲፈጸሙ ብዙወች እንዳላዩ ሆነው አልፈዋቸዋል። በደሴ የጃሪ ህጻናት ማሳደጊያ የተፈጸመውን ግፍ ብዙወች የሚረሱት አይመስለኝም። አንድ ወቅት ባህርዳር ውስጥ አንድ አሮጌ ፈረንጅ ከአንዲት የ16 አመት ልጅ ጋር ሆቴል ውስጥ ሲቀናጣ አይቼ ልጅቱን ቀርቤ ላናግራት ስሞክር ፈረንጁ “አየሃት ሚስቴ በጣም ቆንጆ ነች” አለኝ። ወዲያው አብረውት ተቀምጠው ቢራ የያዙት ያገራችን ወንዶች ፊት ላይ ያየሁት ሳቅ የማደርገውን አሳጣኝ። ይህ አሮጌ ፈረንጅ በራሱ ሃገር ቢሆን ኖሮ ከህጻን ጋር በግልጽ ታይቶ ይቅርና በልጅቱ ጥቆማ ብቻ ሊታሰር ይችል ነበር። እዚህ ግን ተዝናንቶ ሚስቴ ናት ለማለት ያስደፈረው ምንድን ነው? ይቺን ህጻን ከዚህ ሽማግሌ ያቆራኛት ባካባቢው የሰፈነው የነጭ ሉአላዊነትን የተቀበለ አለም ስላለ ነው። ቀርቤ የሆቴሉን ሰራተኛ አነጋገርሁ፣ “ምን እናድርግ፤ እንግዳ ንጉስ ነው፤ ልጅቱ ደሞ እየመጣች ሁሌ እሱ ጋ ታድራለች” አሉኝ። ነገሩን ላሳጥረውና፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄድሁ። በኢትዮጵያ ህግ ህጻናት ጋር ወሲብ መፈጸም ወንጀል ነው፣ ይህን ወንጀል የሚፈጽም ሰውና የሚፈጸምበትን ቦታ ልጠቁም መጥቻለሁ ብየ ሪፖርት አደረግሁ። መርማሪው ተጠርጣሪው ፈረንጅ መሆኑን ሲረዳ የማይረሳኝን መልስ ሰጠኝ። “አየህ አሁን ይህንን ሰው ብይዘው ‘እኛ ኢንቨስተር ለምነን እያመጣን ጥቅም ማግኘት ፈልጋችሁ አሰራችሁት’ ብለው ፖለቲከኞቹ እኛ ላይ ይዞሩብናል፤ ምን ማድረግ እንችላለን?” አለኝ። ባገሬ ላይ ነጮች ወንጀል ሲፈጽሙ ምንም ማድረግ የማልችል መሆኔን ሳይ የተሰማኝን መግለጽ አልችልም። የነጭ ሉአላዊነት በውስታችን ሲነግስ ሃገር በሙሉ ሲዋረድ አይሰማንም።


የነጮች ሉአላዊ ስራት በበርካታ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ባህሪያችን ውስጥ ይንጸባረቃል። ህዝባችንን እንቀይራለን የሚሉት ፖለቲከኞቻችን ሁሉ ርዮተአለማቸውን የሚገለብጡት የነጭ ሉአላዊነት ውስጥ ከፈለቁት ንድፈ ሃሳቦች ነው። በየንግግራቸው ውስጥ እንግሊዝኛ የሚቀላቅሉ ሰወች አማራጭ ቃላት አጥተው ከሆነ ቃላቱን ከተናገሩ በኋላ ትርጉሙን በአማርኛ ለማብራራት ለምን አይሞክሩም? ባስተማራቸው ህዝብ ፊት ሲናገሩ በራሳቸው ቃላት ሃሳባቸውን መግለጽ አለመቻላቸውስ ስለምን አያሳፍራቸውም? ካልን የእውቀታቸው መለኪያ የህዝቡ ግምት ሳይሆን የነጭ ሉአላዊነት ስራት ስለሆነ ነው። ሰው ሃፍረት የሚሰማው የሚያከብረውን ማህበረሰብ ህግ ሲጥስ ነው። የነጭ ሉአላዊነት ስራት ውስጥ ህዝብ እንዲያከብርህ እንጂ ህዝብን እንድታከብር አትገደድም።

ሌላውና አሳሳቢው ያገራችን ሁኔታ ባብዛኛው በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱት ከተማ ተወልደው ያደጉና ገጠር ሂደው አንድ ሳምንት እንኳን ኑረው የማያውቁ ናቸው። ሁሉም ባይባልም፣ ከነዚህ ብዙወቹ ስለገጠሩ የሚያውቁት ነገር ስለሌለ የሚታያቸው አማራጭ የነጮቹ ስራት ብቻ ነው። በሚገርም ሁኔታ ስለአለም ብዙ ይናገራሉ፣ ባገራቸው ይኮራሉ ግን ያገራቸውን 80% በላይ ህዝብ ቀርበው አያውቁትም። ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ ዩንቨርስቲወች ስለተከፈቱ በርከት ያሉ የገጠር ልጆች ትምህርት ቢያገኙም የመጡበትን ህይወት ጠልተውት እንዲወጡ የሚያደርግ ልምድ ቀስመው ነው የሚመረቁት።

የነጭ ሉአላዊነት ስራት መገለጫ ሌላ ምሳሌም እናንሳ። በፈረንጆች ተሰብስቦ የተወሰደው በርካታ የብራና መጻህፍት ጠያቂ አጥቶ ተበትኖ የቀረው የነጮችን ሉአላዊነት የሚያከብር ስርአት ውስጥ ስለምንኖር ነው። እንደውም አንዳንዶች “እንኳን እነሱ ወሰዱት፣ እኛ ጋር ቢቀር እስካሁን ይቀደድ ወይም ይጠፋ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህም የሚያሳየው እነሱ የያዙት የእኛም ነው፤ እኛ ለራሳችን ታሪክ እንኳን አንታመንም የሚል የዝቅተኝነት ስሜትን ነው። የሚያሳዝነው፣ ሰወች ይህንን መናገራቸው ሳይሆን፡ ይህንን እንዲናገሩ ያደረጋቸው ምክንያት መኖሩ ነው።


ዛሬ እውቀት ሁሉ በባለቤትነት በግለሰብ እንዲያዝ የተደረገበት ዘመን ነው። በጤፍ ባለቤትነት ላይ ህጋዊ መብት አለን የሚሉት ፈረንጆች ጉዳይ እስካሁን እምዳልተፈታ ይታወቃል። ከጥቂት አመታት በፊት ጀርመን ውስጥ ያለው ‘የግእዝ አስተማሪ ነኝ’ የሚል ተቋም፣ ትግራይ ከሚገኝ ጉንዳጉንዲት ገዳም ሂዶ ከ2000 በላይ የብራና መጻህፍትን በዲጂታል ሰብስቦ ወዳገሩ ይዞ ሂዷል። የሚገርመው ይህንን ሲያደርግ ፌዴራል ያለውን ቅርስ ጥበቃን እንኳን አላስፈቀደም። ቅርሶች የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን እንደመሆናቸው መንግስት እንደሃገር ሳይፈቅድና ቅጅ እንኳን ሳይወስድ ሰተት ብለው የፈለጉትን ሲወስዱ ነጮችን ማን ይጠራጠራል፣ ማንስ ደፍሮ ይጋፋል? የነጮች ከሆነ ነገር ጋር ቀርቦ ፎቶ መነሳት ክብር የሚመስለው ስንቱ ነው? በእርግጥ ይህ ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተደርጎ የሚቀር ቢሆን ምንም አይደለም፤ አንዱ አንዱን ሊያደንቅ ይችላል። ግን የነጭ ሉአላዊነት በንጹህ አድናቆት ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ ይልቁንም በምኞት ላይ፣ በራስ ወዳድነት ላይ፣ ትልቅና አዋቂ በመምሰል ላይ፣ ሃገር ቤት ካለው ህዝብ ላቅ ብሎ መታየት በመፈለግ ላይ ወዘተ የተመሰረተ ስሜት ነው።


የነጮችን ሉአላዊነት እንደነፍስና ስጋቸው ከራሳቸው ጋር ያዋሃዱ በርካታ ሰወች አሉ። ለእነዚህ ሰወች የራሳቸው ብዙሃን ህዝብ፣ በተለይ ገበሬውና ድሃው፣ የሃገር ባለቤትና ሙሉ ዜጋ መሆኑን እንኳን ረስተውታል። የሚከራከሩለት ሃሳብ ጠቀሜታውና ተገቢነቱ ለማን እንደሆነም አያስቡትም። የሃሳባቸውን ጠቀሜታ የሚመዝኑት ከውጭ ሃገር በኮረጁት ጥቅስ ነው። እነዚህ ሰወች ይህንን የሚያደርጉት ክፉወች ስለሆኑ ግን አይደለም። እርግጥ ጥቅም አሳዳጆች እንዳሉም ግልጽ ነው።፡ሖኖም ጠንክረው የተማሩና ለውጥ የሚፈልጉ ብዙ ሰወች ሳያውቁት የነጮች ሉአላዊነት አገልጋይ ሆነዋል። ምን ያድርጉ? ሰወች እንዳለፉበት የትምህርት ስራት፣ የሃገር ባህልና የኑሮ ፍላጎት የተሻለ የሚመስላቸውን አስተሳሰብ ይይዛሉ። አስቀድመው የሚወለዱበት አለም በነጮች ሉአላዊነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ሃሳባቸውን ለመቀየር የሚችሉበት እድል ከየት ሊያገኙ ይችላሉ? ለዚህ ነው የነጮች ሉአላዊነትን የሚያስከብርን ስራት በራሳችን ላይ የጫንነው ቅኝ አገዛዝ ስራት ነው የምንለው።

(ይቀጥላል)

522 views0 comments

Comments


bottom of page