top of page
Writer's pictureHager Bekel

እርዳታና ብድር የፈጠሩት ዘመናዊ ባርነት



ዘመናዊ ክፋት ምን ማለት ነው? ዘመናዊ ክፋት ማለት የተጎዱ ሰወችን ለመጥቀም በሚል መልካም አላማ ስም የሚፈጸም አንድ ተግባር፣ ጥቂቶችንና ራስን ብቻ ጠቅሞ ብዙወችን ግን በባሰ ችግር ወይም ጭቆና ውስጥ የሚከት ማለት ነው። ከግለሰብ እስከ መንግስታት ድረስ የሚፈጸምባቸው ፈርጀ ብዙ መንገዶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ እርዳታ ነው። እርዳታ እንዴት የጭቆና መሳሪያ ይሆናል? ጉዳዩ ውስብስብ ስለሆነ እስኪ በምሳሌ እንጀምረው።


አንድ ህመም ያለበት ሰው ሃኪም ዘንድ ይሄዳል። ሃኪሙ ተንኮለኛ ስለነበረ በሽተኛው ያለበትን ችግር በቅጡ ሳይጠይቅ የበሽታው ምንጭ የታማሚው ጥፋት እንደሆነ ያሳምነውና መድሃኒት ነገር ይሰጠዋል። በሽተኛው፣ በውድ ዋጋ የገዛውን መድሃኒት ወስዶ ሲጠቀም ትንሽ ይሻለውና መድሃኒቱ ሲያልቅ እንደገና ይብስበታል። ተመልሶ ሃኪሙ ዘንድ ሲሄድ ሃኪሙ አሁንም ተጨማሪ መድሃኒት ይሰጠዋል። በሂደት መድሃኒቱ ሱስ የሚያስይዝ ስለነበረ በሽተኛው ያለውን ንብረት ሁሉ እየሸጠና በእዳ እያስያዘ መድሃኒቱን መውሰድ ይቀጥላል። በዚህ መንገድ የተጎዳው በሽተኛና ሌሎችም እንደሱ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰወች ሃኪሙ ዘንድ ሂደው ገንዘብ ስለጨረሱ በእርዳታ ወይም በብድር መድሃኒት እንዲሰጣቸው ሃኪሙን ይለምኑታል። እሱም እሺ ይልና የመድሃኒቱን ዋጋ ቀንሶ የተቀነሰውን ገንዘብ ‘እርዳታ’ ብሎ ይመዘግብና ይሰጣቸዋል። ብድራቸውን ደግሞ እነሱ መመለስ ባይችሉ በልጅ ልጆቻቸው እንዲከፈል ከተስማሙ ወደፊትም እንደሚሰጣቸው ቃል ይገባላቸዋል። በሽተኞቹም አመስግነውና ተስማምተው፣በልጆቻቸው ስም ፈርመው እየተበደሩ መድሃኒቱን መውሰድ ይቀጥላሉ። ሃኪሙ ታዋቂና ሃብታም ብቻ ሳይሆን መልካም ስም ያለውና ለልጅ ልጅ ልጅ የሚተላለፍ ሃብትና ድርጅት ያለው ሆነ። ወደኋላ ልጆቻቸው ታመው ወደሃኪሙ ሲሄዱ የወላጆቻቸውን የእዳ መዝገብ ያወጣና መታከም የሚችሉት መጀመሪያ የወላጆቻቸውን እዳ መክፈል ከቀጠሉ ብቻ እንደሆነ ይነግራቸውና፣እነሱ የሚታከሙበትን ግን በብድር ሊሰጣቸው እንደሚችል ይነግራቸዋል። አማራጭ የለንም ብለው ስላመኑ እሺ ይላሉ። እሱም የያዙትን ገንዘብ ለወላጆቻቸው እዳ ከነወለዱ መክፈያ እንዲሆን እየተቀበለ፣ የእነሱን ድርሻ ግን በእዳ መዝግቦ፣ እነሱ ሊመልሱት ባይችሉ ለልጅልጆቻቸው እንዲተላለፍ እንዲስማሙ አድርጎ፣ መድሃኒቱን ይሰጣቸዋል። እነሱም ከወደፊት ልጆቻቸው ላይ እዳ እየከመሩ እንደወላጆቻቸው ይቀጥላሉ። ያ ተንኮለኛ ሃኪምም ትልቅ ድርጀት ስለፈጠረ የድርጅቱ ተቀጣሪወችና የሃብቱ ወራሾች እሱ ያደርግ የነበረውን እያደረጉ ይቀጥላሉ። በዚህም የዚያ ሃገር ሰወች ትውልድ፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስ እየወለደና እየተራባ በሚቀጥል የእዳ ባርነት ውስጥ ተዘፍቆ ቀረ።


የዚህን ሃኪም ስራ ዘመናዊ ክፋት ልንለው እንቺላለን። ዘመናዊ ክፋት የጥፋተኝነትን ብይን ወደጉዳተኞች ያዛውራል። ይህ የሚፈጸምበትን የእርዳታ ነገር ዛሬ በትንሹ እንይ።


ብዙ ጊዜ ይህንን ያህል ገንዘብ በእርዳታ ተነኘ ሲባል እንሰማለን። ሆኖም ስለእርዳታ ሲነገር የማንሰማው ብዙ ጉዳይ አለ። እርዳታው የተገኘው ለምን አላማ ነው? ክፍያው የሚከፈለው እንዴትና ለማን ነው? ወዘተ የሚሉትን በዝርዝር አናውቅም።

እርዳታ በሁለት ይከፈላል። አንዱ የሰባዊነት እርዳታ ሲሆን ይህ አይነት እርዳታ የድንገተኛ ችግርን ለመፍታት የሚሰጥ ነው። የድርቅ አደጋን ለመከላከል፣ ረሃብተኞችን ለመርዳት፣ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን ለመርዳትና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚሰጡ እርዳታወች የሰባዊነት እርዳታ (Humanitarian aid) ይባላል። ይህ እርዳታ አሰጣጡ ላይ ችግር ቢኖርበትም በመሰረቱ መልካም እርዳታ ነው። ይሁን እንጅ ከአጠቃላይ የእርዳታ በጀት ለሰባዊነት የሚውለው እርዳታ በአማካይ 1% ብቻ ነው። ይህን እናስተውል። ብዙ ጊዜ እርዳታ ሲባል ለድሆች የሚመጣው ይህ አይነት እርዳታ ይመስለናል።እውነታው ግን አንድ ፐርሰንት ብቻ ነው ለረሃብ፣ ለአደጋ ወዘተ የሚሰጠው። ሌላው 99% እርዳታ የልማት እርዳታ በሚል ስም ነው የሚመጣው። ዋናው ጨዋታ ያለውም እዚህኛው ላይ ነው። የልማት እርዳታ። ምን ማለት ነው?

የልማት እርዳታ ብዙ ጊዜ የሚውለው ለጋሽ ሃገሮች ብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር፣ የድሃ ሃገሮች ኢኮኖሚ የነሱን ጥቅም በሚያስጠብቅ አቅጣጫ እንዲያጓዝና የዲፕሎማሲ ትርፍ ለማግኘት ነው። ለምሳሌ ድሃ ሃገሮች ራሳቸውን ለመቻል ከመጣር ይልቅ በውጭ ምርቶች ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ፣ እድገት ላይ ማለትም የተፈጥሮ ሃብታቸውን ወደውጭ ምንዛሬ መቀየር ላይ እንዲያተኩሩ፣ ሃብትን ለህዝባቸው ከማከፋፈል ይልቅ ሃብትን በጥቂቶች እጅ በመሰብሰብ እድገት እንዲያስመዘግቡ፣ የመንግስት ድርጅቶችን ለግል እንዲያዞሩ፣ ታሪፋቸውን እንዲቀንሱ፣ ገንዘባቸውን ከዶላር የመግዛት አቅም በታች እንዲያወርዱ፣ የአለም የንግድ ድርጅት አባል እንዲሆኑ፣ የውጭ ካምፓኒወች እንዳገርውስጥ ካምፓኒወች እንዲቆጠሩ፣ ጥሬ እቃ ወደውጭ በርካሽ ሽጠው ያለቀ እቃ በውድ እንዲያስገቡ፣ መሬታቸውና ሊላውም ጥሬ ሃብታቸው የውጭ ገበያን ፍላጎት ለማርካት እንዲውል፣ የልማት ስራቸው የነሱ ኩባንያወችና ዜጎች የስራ መፍጠሪያ እንዲሆን፣ የልማት ስራ በመንግስት ሳይሆን በንግድ ድርጅቶች እንዲሰራ ወዘተ ማገዝ ነው። በነሱ ትርጉም ልማት ማለት የነሱን መንገድ መከተል፣ ለእነሱ መገዛት ስለሆነ ይህ አይነቱ የልማት እርዳታ ድህነትን ከመፍታት ይልቅ ኋላቀርነትን አባብሶ ጥገኛ ኢኮኖሚን ይፈጥራል። በተለይም በ1980ቹ ወዲህ ነው ድሃ ሃገሮች የተቋማት ማሻሻያ ፕሮግራም (SAPs) የሚባል የእርዳታና የብድር ቅድመ ሁኔታ እንዲያሟሉ ተጠይቀው በሂደቱም ብዙወቹ የድሃ ህዝባቸውን ፍላጎት አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ወደ ሃብታሞች ካፒታል አገልጋይነት የተቀየሩት።


በዚህ ሂደት ጥቂት ሃፍታሞችና የከተማ ተቀጣሪወች ቢፈጥሩም፣ ሃገራቱ የበለጠ ድሆችና ተቋማዊ ጥገኛወች ሆነዋል። ትምህርትን እንደምሳሌ ብንወስድ ለትምህርት በሚሰጡት ብድር እና እርዳታ አማካኝነት የውጭ ሃገር ቋንቋና የውጭ ሃገር እውቀት ብቻ እንዲስፋፋ በመደረጉ፣ ጥገኛ ማህበረሰብ በመፍጠር በዋናነት የሚጠቀሙት አበዳሪወቹ ሆነዋል። እነሱን ተበድረን የእነሱ አገልጋይ የሚያደርገንን ትምህርት እንማራለን ማለት ነው። የትምህርት መጻህፍት ሲታተሙም ሳይቀር ስራው ለውጭ ተቋራጮች ክፍት እንዲሆን በማስገደድ መጻህፍት እንኳን ሃገርውስጥ እንዳይታተሙ እንቅፋት ይፈጥራሉ። በእርዳታ ስም የሚመጣውን ገንዘብም የራሳቸውን ኤክስፐርቶችና አማካሪወች በብዙ ገንዘብ ቀጥረው በመላክ የእርዳታ ገንዘቡን ለእነሱ ዜጎች የስራ መፍጠሪያ ያደርጉታል። በእርዳታ የሚገዙትን ትላልቅ እቃወች እነሱ ከሚወስኑት ሃገር ወይም ካምፓኒ ብቻ እንዲገዙ ያስገድዳሉ። የእነሱ ሃገር የልማት ኩባንያወች የልማት ስራውን እንዲሰሩት በእርዳታው ውል ላይ ያስገድዳሉ። ለእኛ የተሰጠውን ብድር ለራሳቸው ዜጎች ደሞዝና ወጭ ከፍለው ስራውን ይሰሩና ኋላ ከነወለዱ እኛን ያስከፍላሉ ማለት ነው። በእርዳታው አማካኝነት አንዳንዴም ከሰው ሃገር ገብተው እንደባለስልጣን ያዛሉ፣ ያስፈጽማሉ፣ ይገመግማሉ።


ይህ ሁሉ ሆኖ ሃገር ቢጠቀም ባልከፋ። እርግጥ ጥቂት ጠብታወች እዚህና እዚያ ይታያሉ። ከተማወች ውስጥ የሚያብለጨልጩ ነገሮች ይደረጋሉ። እኛም ያጣነውን ስለማናውቅ፣ ባገኘናት ትንሽ ነገር ተደስተን እጅ እንነሳለን፤ ሌላም እርዳታ እንዲሰጠን እንጠቃለን። አብዛኛው የእርዳታ ገንዘብ ግን በስማቸው ከተላከላቸው ድሃ ህዝቦች አይደርስም። እድገት ይጨምራል፣ ድህነት ግን አይቀንስም፤ እርዳታ ሰጭወቹ ስምና ዝና ያተርፋሉ፤ የማይፈልጉትን ሸቀጥ ያስወግዳሉ፤ በእርዳታው ሳቢያ ባለማቀፍ መድረኮች ላይ የተሻለ ‘ቲፎዞ’ ይፈጥራሉ።


እርዳታ ብለን ከምንጠራው 99% የሚውለው ብዙ ጊዜ ህዝብንና ሃገርን የውጭ ጥገኛ በሚያደርግ ተግባር ላይ ነው ብለናል። ገንዘቡን አበድረውህ እንደፈለግህ አድርገው አይሉህም፤ ከሰፈር አማካሪ ቢሮ ከፍተው እቅድህን ይሰሩልሃል። ገንዘቡን ከነስራው እቅድና አሰራሩ ጭምር በራሳቸው ቋንቋ ጽፈው ይሰጡሃል። አዲስ እቅድ ይዘህ ሳይሆን የእነሱን ሰነድ በትንሹ አሻሽለህ ስትመልስ፣ እሺ ካሉህ ድል ያደረግህ ይመስልሃል። እየሳቁብህ ያሞካሹሃል። በእለቱ በሚፈጠረው ሞቅታ የወደፊቱን ለቅሶ ትረሳና ሰነዱን ትፈርማለህ። ህዝብህ ላይ የነሱን ፍላጎት ለመጫን የሚችሉብህ እቃ ያደርጉሃል ማለት ነው።


ተቋማዊ ክፋት


ከላይ የተገለጸውን የሚያስፈጽሙበትን አለማቀፋዊ አደረጃጀት ተቋማዊ ክፋት ልንለው እንችላለን። ብድሩ በቀጥታ ከአንድ መንግስት ወይም ከመንግስታት ድርጅት ሊገኝ ይችላል። ከአበዳሪወቹ ውስጥ ሰለስቱ እርኩሳን (unholy trinity) የሚባሉት የአለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍና፣ የአለም ንግድ ድርጅት የሚሰጡት እርዳታ ከሁሉም አስከፊ ጥገኝነትን ይፈጥራል። እነዚህ ድርጅቶች አላማቸው የአንድን ሃገር የገንዘብ ስርአት የኢኮኖሚ ሉአላዊነትን መቆጣጠር ነው። እነዚህ ትልልቅ የአክስዮን ድርሻ ባላቸው ውስን ሃፍታም ሃገራት የሚመሩ ተቋማት፣ ለስሙ አለማቀፍ ይባላሉ። አለም ባንክ ውስጥ 189 ሃገራት አባል ናቸው። አሜሪካ 16.51% የአክስዮን ድምጽ አላት፣ የብዙ ድሃ ሃገሮች የተናጥል ድምጽ ግን፣ ግማሽ ፐርሰንት እንኳን አይሞላም። ኢትዮጵያ ያላት 0.09% ነው። በዚህ ድምጽ ምንም ማስወሰን አትችልም።


እነዚህ ድርጅቶች ዋና ተግባራቸው የሃገሮችን ኢኮኖሚ ማስተዳደር ነው፤ የእርዳታ ሳይሆን የአስተዳደር (governance) ድርጅቶች ናቸው። ይህንን ልብ እንበል። ኢኮኖሚውን ከህዝብ የተመረጠ መንግስት የሚያዝበት ቢሆንም እነዚህ ተቋማት ከላይ ሆነው የመንግስታትን የገንዘብና የኢኮኖሚ ውሳኔ ይዘውራሉ። በዝቅተኛ ወለድ የሚያበድሩትን ገንዘብ (concessional loans) ሳይቀር ለወሬ እንዲመች ‘እርዳታ’ ብለው ይጠሩታል። የብድር ማሻሻያ ካደረጉ፣ የመክፈያ ጊዜ ካራዘሙ፣ ድርጊታቸው ያመጣው ለውጥ ካለ ቶሎ ብለው ‘እርዳታ ተሰጠ” ይላሉ። በእርዳታ የሚኮሩ መንግስታትም ብድሩን ሁሉ እርዳታ ለማለት ይዳዳቸዋል። ነጻ ዶላር ከውጭ እንዳመጡ በማስወራት በህዝባቸው ፊት አለማቀፍ የሆነ ተጽኖ ፈጣሪነት እንዳላቸው ለማሳየት ይጥራሉ። በሃያላን መንግስታት የሚመሩት የገንዘብ ተቋማት እርዳታ ወይም ብድር የደም ስራቸው ነው፤ ብድር መስጠት ካቆሙ ወይም ያበደሩት ገንዘብ ጠቅላላ ከተመለሰላቸው ከገበያ ይወጣሉ። ለዚህ ነው፣ ሃገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ ሲገጥማቸውና የተበደሩትን መመለስ ሲያቅታቸው ተጨማሪ ብዙ ብድር የሚያስታቅፏቸው። የሚያበድሩበት መንገድም ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ትርፍ (ROR) የሚያስገኝላቸው መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ነው።


እርዳታ የሚያገለግለው ሌላም ጥቅም አለ። በእርዳታ የሚመጣ ገንዘብ ጥብቅ ቁጥጥር አይደረግበትም፤ ትንሽ እርዳታ ጣል የሚያደርጉ ሃገራትና ድርጅቶች ይታመናሉ፣ ስራ ሲሰሩ እንዳያጭበረብሩ በሚል ጠንካራ ቁጥጥር አይደረግባቸውም። እንደጥቅመኛ ሳይሆን እንደ አጋዥ ጓደኛ ይታያሉ። እውነታው ግን እርዳታ ተቀባዮቹ እነሱ እንጅ ድሃ ሃገሮች አይደሉም። አንድ በጥናት አይ የተመሰረተ ምሳሌ እንይ። በ2012 ከሃፍታም ሃገሮች ወደድሆቹ የገባው የውጭ እርዳታና ኢንቨስትመንት ገንዘብ መጠን 1.3 ቲሪሊፖን ዶላር ነበር ይለናል። ታዲያ በዚያው አመት ከድሆቹ ወደሃብታሞቹ የወጣው 3.3ቲሪሊዮን ነበረ። ይህ ማለት ድሃ ሃግሮች ለሃብታሞቹ የ2 ቲሪሊዪን ዶላር ብልጫ ያለው ሃብት ሰጥተዋል ማለት ነው። ከ1980 ጀምሮ ብንቆጥር፣ ከድሃ ሃገሮች የወጣውን ገንዘብ ከገባው ስንቀንስ፣ ድሃ ሃገሮች የተጣራ 16.3ቲሪሎዮን ዶላር ተወስዶባቸዋል። ይህ ሁኔታ የእጃዙር እርዳታ (aid in reverse) ይባላል። ድሆች ለሃፍታሞች እርዳታ የሚሰጡበት አሰራር ማለት ነው። ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚዘረፈው እንዴት ነው? ሌላው ቀርቶ ከብድር ወለድ ብቻ በቀጥታ ለሃብታም ሃገሮች ባንኮች በዶላር የተከፈሉት 4.2 ቲሪሊዮን ነበር፤ ይህ በእርዳታ ወደድሆቹ ከገባው በብዙ እጅ ይበልጣል።ይህ ማለት ድሃ ሃገሮች ጥሬ እቃ ብቻ ሳይሆን ዶላርም ለሃብታሞቹ ይሰጣሉ ማለት ነው።


ሌላው የሃብታም ሃገር ኩባንያወች ድሃ ሃገር ሲሄዱ ትክክለኛ ግብር አይከፍሉም። ብዙ ጊዜም ሃገራቸውን ትተው ድሃ ሃገር ፋብሪካ የሚከፍቱት በቀላሉ የሚበዘብዙት ህዝብና የሚሸውዱት መንግስት እንዳለ ስለሚያውቁ ነው። የውሸት ድርጅት (tax havens) ሌሎች ድሃ ሃገሮች ውስጥ አቋቁመው ገቢያቸውን ዝቅ በማድረግ ኢምንት ግብር እየከፈሉ የሚዘገንን ሌብነት ይፈጽማሉ። ከ1980 ጀምሮ 13.4ቲሪሊዮን ያልተመዘገበ የካፒታል ዝርፊያ ፈጽመዋል። የሚገርመው የሚያደርጉት ዝርፊያ እየተጋለጠም ጭምር በመቀጠል ላይ ናቸው። ለምሳሌ አንጎላን እንውሰድ፤ ከኩየት የበለጠ ነዳጅ ታመርታለች፣ እንቁና ወርቅ ሞልቷታል፤ የኢኮኖሚ እድገቷ በጥቂቶች የተያዘ ስለሆነ በተለይ 30% የሚሆነው ህዝብ ሙልጭ ያለ ድሃ ነው። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ልጅ ኢዛቤል ዶስ ሳንቶስ ደሞ ከአፍሪካ ሴቶች በሃብት አንደኛ ስትሆን፣ የከበረችው ህዝቡን ከውጭ ካምፓኒወች ጋር በመሻረክ ሙልጭ አድርጋ ዘርፋ ነው። የውጭ ኩባንያወች ድሃ ሃገሮች ውስጥ ኢንቨስትመንት አካሂደውና የተፈጥሮ ሃብት አውድመው ትርፋቸውን ወዳገራቸው ይወስዳሉ።


ሌላው በተለይ በአፍሪካ ሃገሮች በሙስና የተጨማለቀ ስራት ሲፈጠር ብዙ የውጭ ኩባንያወች ደስ እንደሚላቸው በጥናት ተረጋግጧል። ለምሳሌ ጄምስ ፈርጉሰን ባጠናው ጥናት ያሳየው ከፍተኛ የሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸው የሰሃራ በታች ሃገሮች በሙስናና በጨቋኝነት ቁንጮ የሚሰለፉት ናቸው። ድቡብ አፍሪካን ሳይጨምር ከ1994-5 ባለው ጊዜ ከሰሃራ በታች ወዳሉት ሃገሮች ከገባው የኢንቨስትመንት ሃብት 50% ያህሉ ከፍተኛ ሙሰኝነት ወዳለባቸው ሃገሮች የገባ ነበር። በነዚህ ሃገሮች ውስጥ በሃብታም ሃገሮች እንደሚደረገው፣ ካምባኒወችን የሚቆጣጠር ጠንካራ ህግ የለም። ካምፓኒወች ትርፋቸውን ላካባቢው ህዝብ እንዲያወጡና ከፍ ያለ ግብር እንዲከፍሉ አይገደዱም። መንግስቶቹ የነሱ የግል ቅጥረኛ የሆኑ ያህል የሚፈልጉትን በትንሽ ክፍያ ይፈጽሙላቸዋል። መሬት የሌላቸው አፍሪካውያን በሞሉበት አህጉር ውስጥ በ2006 ከ10-20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኢንቨስትመንት ስም ወደከበርቴወቹ ተላልፎ ይሄው እስካሁን ለድሆቹ ያመጣው ለውጥ የለም። እንደውም መሬቱን ለመጠበቅ የአካባቢና የተፈጥሮ ሃብት ልይ ቁጥጥር አያጋጥማቸውም። ባጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ ከነሱ የትርፍ ፍላጎት አንጻር ውጤታማ (ኤፊሸንት) ነው። ዊልያም ሬኖ ይህንን የሽፍቶች ፖለቲካ (warlord politics) ይለዋል። ብዙ ጊዜ ህዝብን ከልቡ የሚያገለግል መንግስት ከነሱ የትርፍ ፍላጎት ጋር ይጋጫል። ለዚህ ነው አንዳንዴ እነዚህ ካምፓኒወች መንግስት በተቃዋሚ ድርጅቶች እርምጃ እንዲወስድ በድብቅ ሲገፋፉ የሚታዩት። ለምሳሌ የሸል ካምፓኒ የኦጎኒ ጎሳወች ላይ የናይጀሪያ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ይጎተጉቱ ነበር። መሬታችንን ነዳጅ እየደፉበት ወንዛችንን በከሉት፣ አካባቢያችንን አጠፉት፣ ስራም አላገኝንም ብለው ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። መንግስት ተቃውሞውን ለማስቆም ሲነሳ የሸል ሄሊኮፕተሮች ለመንግስት መሳሪያና ማጓጓዣ በማቀበል ጭምር ተባበሩ። የተቃውሞው አነሳሾች ታዋቂውን ገጣሚ ሳራዊዎ ጨምሮ 9 የጎሳ መሪወች በናይጀሪያ መንግስት በስቅላት እንዲገደሉ አስደረጉ። ይህንን ሁሉ አድርገው ባጋጣሚ ሼል በሃገሩ ክስ ተመስርቶበት ወንጀሉ ለአለም ሲጋለጥ የ15.5ሚሊዮን ዶላር አፍ መያዣ ካሳ ከፍሎ ጉዳዩ እንዲረሳ አስደረገ።


ይህንን ሁሉ የምንለው የእኛ ሳይበቃ የመጭውን ትውልድ ተስፋ አጨልመን እንዳናልፍ እንድንጠነቀቅ ነው። እያንዳንዷ ብድር ከእያንዳንዱ ልጅ ትከሻ ላይ የምንጭነው ሸክም ናት። ነፍስ ላላወቁ ልጆቻችን የኢኮኖሚ ባርነትን ማውረስ አለብን? የልማት እርዳታ እዳችንን ለመክፈል ያለንን እድል በማጨለም የኢኮኖሚ ባርነቱ ሊያስቀጥል ይችላል። ልማት ዘላቂ የሚሆነው ራሳችን የምንቆጣጠረው ሲሆን እንጅ ለምነን የምናመጣው ሲሆን አይደለም። የነሱን ዶላር ከእኛ ህዝብና ሃብት አስበልጠን ዋጋ መስጠት የለብንም። የውጭ ኢንቨስትመንት ስንፈቅድ ከነሱ የምንሰበስበው ገቢ ግልጽ በሆነ አሰራር ወደድሃው ህይወት ውስጥ እንዴት እንደደረሰ የማሳየት ሃላፊነት አለብን። ይህንን ካላደረግን የምናገለግለው የባእዳንን ካፒታል እንጅ የህዝባችንን ፍላጎት አይደለም ማለት ነው።


ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የማይቻል ግን አይደለም። ዞሮ ዞሮ ህዝባችን እስካሁንም ያለው ወደፊትም የሚኖረው በነሱ ላይ ተንጠልጥሎ አይደለም። ከገንዘብ ሃይል የበለጠ የሰው ህይወት ውስጥ ታላቅ ሃይል አለ። መጀመሪያ ግን ችግሩን ጥርት አድርጎ ማወቅ ያስፈልጋል። ከባእዳን የገንዘብ እስራት ለመፈታት ፈጣሪ በነጻ ወደሰጠን ያገራችን እሴቶች ፊታችንን ማዞር አለብን፤ ለራሳችን ዋጋ የምንሰጠው ራሳችን መሆን አለብን። የምንከተለው የኩረጃ መንገድ ወደማንወጣው ቁልቁለት የሚያደርስ ነውና ወደራሳችን ጉዳይ እንመለስ። በዚህ ከቀተልን እርግጥ ነው፣ አሁንም ጥቂቶች ምንም አይሆኑም፤ የተንደላቀቀ ህይወት ይጠብቃቸዋል። ድሆች ላይ የሚደርሰው ግፍ ግን ከጊዜ ጊዜ ይጨምራል። ስለዚህ ወጣቶቻችን የሚበዘብዛቸውን ስራት ሳይሆን እጃቸውን፣ አካባቢያቸውን፣ ራሳቸውን ማመን አለባቸው፤ ህይወታቸው የሚቀየረው በሚሰሩት ስራ እንጅ በሚያምኑት ሃሳብ አይደለም። ለውጥ የሚመነጨው፣ ውሃ የሚጎለብተው፣ አረም የሚነቀለው ከአካባቢ ነውና፣ አካባቢያዊ ትብብር ይጠናከር።


ሃገርበቀል እውቀት የህልውና መሰረት ነው!


ጠቃሚ ማጣቀሻወች


• Assie-Lumumba, N. (2006). Higher Education in Africa : Crises, Reforms and Transformation. Dakar, CODESRIA.


• Brock-Utne, B. (2000). Whose Education for All? The Recolonization of the African Mind. New York: Falmer Press.


• Crewe, E. and E. Harrison (1998). Whose Development: An Ethnogrpahy of Aid. London and New York, Zed Books.


• Ferguson, J. (2006). Global Shadows : Africa in the Neoliberal Order. Durham and London, Duke University Press.



• Parekh, B. (1995). Liberallism and Colonialism : a critique of Locke and Mill. The Decolonistion of Imagination : culture, knowledge and power. J. N. Pieterse and B. Parekh. London and New Jersey, Zed Books.


• Reno, William. Warlord politics and African states. Lynne Rienner Publishers, 1999.


• Woldeyes, Yirga Gelaw. "An East African perspective for paradigm shift on maritime security in the Indian Ocean Region." Journal of the Indian Ocean Region 11.1 (2015): 121-133. https://doi.org/10.1080/19480881.2015.1022018

284 views0 comments

Comments


bottom of page