ግርማ አውግቸው ደመቀ
በኢትዮጵያ በርካታ አቆጣጠሮች አሉ። ከሲቪሉ አቆጣጠር በተጨማሪ፣ ባህላዊ እንዲሁም ከሀይማኖት ጋር የተያያዙ አቆጣጠሮች አሉ። በባህላዊ ረገድ የሲዳማውና በቦረና ኦሮሞ ዘንድ ያሉትን አቆጣጠሮች መጥቀስ ይቻላል።1 ለኋለኛው ምሳሌ የእስልምናውን አቆጣጠር መጥቀስ ይቻላል። የእስልምና ተከታዩ ህዝብ የሀይማኖቱን በዓላት፣ አፅዋማትና ባጠቃላይ ከእስልምና ጋር የተያያዙ የእምነት ጉዳዮቹን የሚያከናውነው በእስልምናው አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናም አብዛኛው በዓላት በሲቪሉ አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ የሚከበር ቢሆንም ተንቀሳቃሽ በዓላቱ የሚሰሉበት የተለየ ቀመር አለ። በዚህ ላይ ብዙ ስራዎች አሉና እነሱን ይመልከቱ። ለምሳሌ፣ በአማርኛ ከተፃፉት ውስጥ የሚከተሉትን ይመልከቱ፤ ጌታቸው ኃይሌ (2006) እና አለቃ ያሬድ (2004)። በእንግሊዝኛ ከተሰሩት ውስጥ ደግሞ ኒውጌባወርን (1964፣ 1979፣ 1988፣ 1989) ይመልከቱ። በዚህ ስራ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ስንል ሌላ ተቀፅላ እስካላስገባንበት ድረስ፣ የሲቪል አቆጣጠሩን ማለታችን ነው።
ይህ መጣጥፍ ዘመን አቆጣጠር የቀናትና የወራት ስያሜ በሚል በግሪጎርያን አቆጣጠር 2016 በሬድ ሲ ፕረስ ካሳተምኩት መፅሀፍ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎበት የተወሰደ ነው። በዚህ መጣጥፍ ለጠቀስኳቸው ዋቢዎች ሙሉ መረጃ እና ለሰፊ ግንዛቤ መፅሀፉን ይመልከቱ። በዚህ ስራ የተሰጡት ዓመቶች በግልፅ ካልተጠቀሱ በስተቀር የግሪጎሪያኑን የሚመለከቱ ናቸው።
Comments